Interview

ሰፊ ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ሩት ሊካሣ ጋራ ... ስለቆዳችን እንክብካቤ

ሰፊ ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ሩት ሊካሣ ጋራ ... ስለቆዳችን እንክብካቤ ብዙ የሚሉት አላቸው፡፡ ዶ/ር ሩት ሊካሣ ያለችዎትን የተጣበበ ሰዓት አብቃቅተው ለዚህ ቃለ መጠይቅ ስለተባበሩን በፋርማኔት መፅሔት ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ፋርማኔት፡- ያልዎትን የትምህርት ደረጃ፣ አሁን የት እንደሚሰሩና ምን ምን እየሰሩ እንደሉ በአጭረ ቢገልፁልን?

የትምህርት ደረጃዬ የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስት ነኝ፡፡ በአሁን ጊዜ በግል ክሊኒክ ውስጥ ነው የቆዳ ሕክምና አገልግሎት የምሰጠው፡፡ ሌሎችም ልሰራ ያሰብኩዋቸውን የግል ስራም በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡

ፋርማኔት፡- ቆዳችን ለሰውነታችን ምን ዓይነት ጥቅሞችን ይሰጣል? ቆዳችን ጤነኛ ነው ማለት የሚያስችለንስ ምን ምን ነገሮችን አሟልቶ ሲገኝ ነው?

ቆዳችን ሰውነታችንን በአጠቃላይ የሚሸፍን በጣም አስፈላጊ የአካል ክፍል ነው፡፡ ከሰዎች ጋር የምንገናኝበትና የምንግባበት ነገር ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ቆዳችን ከተለያዩ ነገሮች ሰውነታችንን ይከላከልልናል። ለምሳሌ ከፀሐይ፣ ከተለያዩ ኬሚካሎች፣ ጀርሞች እና ሌሎችም ጐጂ ነገሮች ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ለሕይወታችን አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ዋነኛ የሆነው ውሃ ከሰውነታችን ውሰጥ እንዳይተን ይጠብቅልናል። በተጨማሪም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች/Electrolytes እንዳይወጣ ይጠብቅልናል፡፡ በተጨማሪም የሰውነታችን የሙቀት መጠን በትክክለኛ ሁኔታ እንዲጠበቅ ከማድረጉ በላይ፣ የሰውነታችን የስሜት ሕዋሳትን ያካተተ በመሆኑ የተለያዩ ስሜታችን እንድንረዳ ይረዳናል፤ በማለት ባጭሩ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ሆኖም ሌሎች በጣም ብዙ አገልግሎቶች አሉት፡፡

ፋርማኔት፡- የቆዳ በሽታ ሲባል ምን ምንን ያካትታል መንስኤዎቹስ ከውስጥ ጤንነት ችግር ጋር ይያያዛልን?

የቆዳ በሽታ ሲባል ብዙ ነገርን ያካትታል ቆዳችን ከሰውነታችን ትልቁ ክፍል ነው። በዚህ ላይ በጣም ተጋላጭነት አለው፡፡ ስለዚህ ቆዳችንን በጣም ብዙ አይነት የውስጥ ችግሮችም መገለጫ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን በቀላሉ ለመግለጽ ያክል በሚከተሉት አይነት መክፈል ይቻላል፡-

  1. በተለያዩ ጀርሞች ምክንያት ማለትም በፈንገስ፣ በባክቴሪያ፣ በቫይረስ እና በተለያዩ ትላትሎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
  2. በአውቶ ኢሚዮን (Autoimmune) ምክንያት የ ሚ መ ጡ / የ ሰ ው ነ ት የመከላከያ ሕዋስ የሰውነት ክፍል በመቃወም ምክንያት የሚከሰቱትን ማለታችን ነው፡፡/
  3. እንደ ሶሪያሲስ (Psoriasis) እና መሰል ችግሮች፡ - የተለያዩ አይነት ኢክዜማ/ Eczema ማለትም በአማርኛ ችፌ የሚባለው ችግር በጣም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው፡፡
  4. ቡግር፡- ደግሞ በፊት ላይ በተደጋጋሚ ከሚከሰቱ ችግሮች አንዱ ነው።

ከዚህ ሌላ ደግሞ በውስጥ ደዌዎች ምክንያት በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችም አሉ፡፡ የተለያዩ የውስጥ ችግሮች የተለያየ የቆዳ ችግር ያስከትላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቆዳ ችግር የውስጥ ችግር መገለጫ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለምሳሌ በጉበት ችግር የተነሳ የተለያዪ የቆዳ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡

ፋርማኔት፡- በአሁኑ ወቅት በቆዳ ላይ የሚወጡ ችግሮች በዓይነታቸውና በስፋታቸው እየጨመሩ ይገኛል፡ ዶ/ር እነዚህ ችግሮች በተለየ የሚያጠቁት የህብረተሰብ ክፍል አለን? ለመከላከልስ የሚያስፈልጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

ይሄ ጥያቄ በጣም ሰፊ ነው ምክንያቱም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የሚከሰተው ችግር የተለያዩ ስለሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በልጆች ላይ ብዙ የፈንገስና የጀርም በሽታዎች ይበዛሉ፡፡ ይህ ግን የሆነው በሕዝብ ብዛትና በተጨናነቀ ሁኔታ ከመኖር የተነሳ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ከፀሐይ የተነሳ የሚመጡ ችግሮች በአሁኑ ወቅት በብዙ ሰው ላይ ያለ ችግር ነው። ይህም ካለው የሙቀት ሐይል መጨመር የተነሳ የሚመጣ ነው፡ ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎች አለአግባብ የተለያዩ መድሐኒቶችን ያሳምረናል በሚል በመጠቀማቸው ምክንያት ብዙ ችግሮች በፊታቸው ላይ ይታያል፡፡

ስለዚህም ማድረግ ካለብን ቅድመ ጥንቃቄዎች ውስጥ ንፅህና መጠበቅ፣ የግል መገልገያዎች በጋራ አለመጠቀም እና ፀሐይን በተለያዩ መልኩ መከላከል ስለሚቻል ጥንቃቄ መደረግ መልካም ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በሐኪም ያልታዘዙ መድሐኒቶችን አለመጠቀም ነው፡፡

ፋርማኔት፡- ብዙ ሰዎች በተለየ መልኩ ለፊታቸው ቆዳ ሲጨነቁ ይስተዋላል፡፡ ዶ/ር በእርግጥ ይህ የሰውነት ክፍል ብቻ ነው የተለየ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ወይስ አጠቃላይ የሰውነታችን ቆዳ ነው?

ቆዳችን በአጠቃላይ የራሱ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ሆኖም የፊት ቆዳ የተለየ ጥንቃቄ ቢደረግለት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የመዳፍና የእግር ቆዳ በጣም ጠንካራ ናቸው ብዙ ነገር ቶሎ አይጐዳቸውም። የፊት ቆዳ ግን በጣም ስስ ነው። ስለዚህም ጥንቃቄ ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ፊታችን ዋና በሚታይ አካላችን ነው፡፡ ሰዎች እኛን ሲያስቡ የሚያስቡት ፊታችንን ነው፡፡ የፊት ቆዳችን ችግር ካለበት ደግሞ በራስ መተማመንን ይቀንሳል፡ ፡ ስራ ቀጣሪዎች እንኳን ንፁሕ ፊት እንዲኖር ይፈልጋሉ። ይህን ሁሉ ስናስብ መጨነቁ አስፈላጊ ባይሆንም ተገቢውን ጥንቃቄ ለፊት ማድረግ ተገቢ ነው። ሆኖም ሌላው ቆዳችን በሙሉ የራሱ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡

 

ፋርማኔት፡- አንዳንድ ጊዜ ቀን ቀን ከፍተኛ የሆነ የፀሐይ ሙቀትና ጨረር ይኖራል፤ ይህ ሙቀትና ጨረር በቆዳ ላይ የሚያስከትለውን አደጋና ችግር እንዴት ይገልፁታል? ህብረተሰቡስ ይህን ለመከላከል ማድረግ ያለበት ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

በተቻለ መጠን ያለባለሙያ ምክር መድሐኒትን በተለይም ጠንካራ የሆኑትን መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ግን አንዳንድ ለመሸጥ የተፈቀዱ አሉ ለምሳሌ እንደ ፈንገስ መድሐኒቶች አንዳንድ አንቲባዮቲኮች ገዝቶ መጠቀም ይቻላል፡፡ ሆኖም ያለሀኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ በተለይ እንደ ቤትኖቬት ያሉ ኮርቲሶን ቅባቶች ቆዳ ላይ ጸጉር የማብቀል፣ የማሳሳት፣ የመቅላት፣ ብጉር የማስወጣት ጉዳት አላቸው፡፡

ፋርማኔት፡- በእኛ ሀገር በአብዛኛው ጊዜ ቆዳችን ላይ ችግር ከደረሰ በኋላ ነው እንጂ ጤነኛ እያለ በህክምና ባለሙያ የታገዘ እንክብካቤና ክትትል አናደርግለትም። ይህን ሁኔታ እንዴት ያብራሩታል? ክትትል ካስፈለገስ አንድ ሰው በየስንት ጊዜው ነው ቆዳ ሐኪም ጋር ቀርቦ መታየት ያለበት ይህን አገልግሎትስ የት ማግኘት ይችላል?

 

እውነቱን ለመናገር በእኛ አገር ሰው ብዙ ችግር እያለው ሳይታመም ቆዳ ሐኪም ጋር መምጣት ያለበት አይመስለኝም። ሆኖም የጠቅላላ ጤናውን ለመጠበቅ በሚደረገው ክትትል ጊዜ ሀኪሞች የሰውን ሁለንተና ስለሚመረምሩ ቆዳም የአካል አንዱ ክፍል ስለሆነ በዚያው ቢጠቃለል ይሻላል፡፡

 ፋርማኔት፡- በአደጉት ሀገራት የቆዳ ካንሰር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህ የቆዳ ችግር በእኛስ ሀገር ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል ችግሩ ከመከሰቱ በፊትስ ማወቅ የሚቻልበት ምርመራ በእኛ ሀገር ይሰጣልን ችግሩንስ ቀድሞ እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቀድሜ እንደተናገርኩት የቆዳ ካንሰር በእኛ ቆዳ የተለመደ ችግር አይደለም ይህም የሆነበት ምክንያት በእግዚአብሔር የተሰጠን የቆዳ ቀለም በእኛ አየር ንብረት ለመኖር እንድችል ስለሆነ ቀለማችን የቆዳ ካንሰርን እንዳይይዘን ይከላከልልናል። ሆኖም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የቆዳ ካንሰር በሽታዎች ስላሉ ምክንያቱ ያልታወቀ የሚቆይ የቆዳ ችግር ሲያጋጥም ባለሞያ ማማከር መልካም ነው፡፡

image
image

ፋርማኔት፡- አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተፈጥሮአዊ የሆኑና በቤቱ ውስጥ ሊያዘጋጃቸው የሚችሉ የቆዳ መንከባከብያ መንገዶችን ከመጠቀም ይልቅ በተለያዩ ካምፖኒዎች የተመረቱ መዋቢያዎችን (Cosmetics) ይጠቀማሉ፡፡ እስቲ እነዚህን ሁለት ነገሮች አጠር አድርገው በማነፃፀር ያላቸውን ጥቅሞና ጉዳት ይግለፁልን?

በእኔ አስተያየት የቆዳውን ውበት መጠበቅ የሚፈልግ ሰው በአጠቃላይ ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መፈፀም አለበት። ማለትም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ በተለይ ፍራፍሬና አትክልት ማብዛት፣ ሌላው ደግሞ ተገቢ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይህም የቆዳን የደም ዝውውር ስለሚጨምር ለቆዳ ጤንነት አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ አልፎ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ በራስ ተነሳሽነት በማስዋቢያ/ Cosmetics ስም ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ እንደ Betnouate ያሉ መድሐኒቶችን አለመጠቀም ይመከራል፡፡ ከዚያም ሌላ ምንነቱ የማይታወቅ ማዲያት ማጥፊያ ሙሽራ ማስዋቢያ እየተባሉ ጥቅም ላይ የሚያውሉት ደግሞ ህገ ወጥነትና ወንጀልም ነው። ስለዚህ ሕብረተሰቡ ከአጓጉል ድርጊት ራሱን ቢጠብቅ ጥሩ ነው፡፡ በተረፈ እውነተኛ ቆዳውን የማይቀየሩና በማይጐዱ በማስዋቢያ/Cosmetics መጠቀም ጥራቱን የጠበቁ እስከሆነ ድረስ ይቻላል፡፡ መድሐኒቶች እና ሕገወጥ ነገሮች ሁሉ ግን በማስዋቢያ/ Cosmetics አይደሉም፡፡

ፋርማኔት፡- ለአንዳንድ የጤና ችግሮች ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች በቆዳ ላይ የተለያዩ ችግሮችን ሲያስከትሉ ይስተዋላል ይህንን ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል?

መድሐኒቶች አንዳንዴ ቆዳ ላይ ጉዳት ያስከትላሉ ይህንም ሕብረተሰቡም ሆነ እኛ ባለሙያዎች መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ መድሐኒት ስናዝ የሚያመጣውን ጉዳት በግልፅ ማወቅ አለብን ካላወቅንም ማንበብ ይጠበቅብናል፡፡ አንዳንዴ በመድኃኒት ምክንያት ሕይወት እስከማለፍ የሚያደርሱ ከባድ የቆዳ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። በተጨማሪም ብዙ አይነት ሌሎች የቆዳ ችግሮች ስላሉ መድሐኒቶች የቆዳ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለዚህም ያልተለመደና ያልተጠበቀ ነገር ሲያጋጥም ባለሙያ ማመከር ያስፈልጋል፡፡

ፋርማኔት፡- በህክምናው ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ የቆዳን እንክብካቤ በተመለከተ ያዘጋጁት መጽሐፍ አለ፡፡ እስኪ ስለመጽሐፉ ይዘት ጥቂት ቢያብራሩልን?

መጽሐፍዋ በጣም ትንሽ ናት። አላማዋ ሕዝቡ ስለፊት ቆዳ ያለውን ግንዛቤና እውቀት ለማዳበር የተፃፈች ናት፡፡ ስለሆነም ስለቆዳችን አሠራር ባአጭሩ ትገልጣለች፡፡ ደግሞ የፊታችን የቆዳ አይነት ምን አይነት እንደሆነና ለእያንዳንዱ የፊት የቆዳ አይነት መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ትገልፃለች፤ በተጨማሪም በተደጋጋሚ ፊት ላይ በሚከሰቱ ችግሮችን አካታለች፡፡ አንዳንድ በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎችም መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም መጽሐፍም ራስን ለማከም የምታስሞክር ባትሆንም በራሳችን ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ እንክብካቤ አካታለች፡ ፡ ከሕዝብ የደረሰኝ ማበረታቻ ወደፊት በዚህ መልኩ እንድገፋበት አበረታቶኛል፡፡

ፋርማኔት፡- እርስዎ የቆዳዎትን ጤንነት ለመንከባከብ በተለየ መልኩ የሚጠቀሙባቸው ነገሮችና መንገዶች አሉ፡፡ እስኪ ለህዝቡ ይህንን ነገር ግልፅ ቢያደርጉልን?

በግሌ የምጠቀመው የተለየ ነገር የለም እንደቆዳዬ አይነት ጥንቃቄ አደርጋለሁ፡፡ ደረቅ ቆዳ ስላለኝ ሳሙና አልጠቀምም ቅባት ብዙውን ጊዜ ኒቪያና መሰል ክሬሞች እቀባለሁ። ፀሐይ መከላከያም እጠቀማለሁ፡፡ ከዚህ የተለየ የማደርገው ነገር የለም፡፡

ፋርማኔት፡- የራስዎ የሆነ የቆዳ ህክምና ክሊኒክ አለዎት እስቲ ምን ምን አይነት አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ እንደሚሰጠ ቢገልፁልን?

ራሴ ባቋቋምኩት የግል የሕክምና ክሊኒክ ውስጥ ነው የምሠራው የምንሠጣቸው አገልግሎት ሕብረተሰቡን ሁሉ ያካተተ የቆዳ ሕክምና ነው። ለሕፃናት፣ ለወጣቶች እና ለአዋቂዎች ሕክምና እንሰጣለን፡፡ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችና ላብራቶሪ የመሳሰሉትንም ያካትታል፡፡ Cryotherapy/ ክራዮቴራፒ አገልግሎት አለን፡፡ ክሊኒኩ የሙሉ ቀን አገልግሎት ይሰጣል፡፡

 

ፋርማኔት፡- በመጨረሻም ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለን?

 

ለሕብረተሰቡ የማስተላልፈው መልእክት የቆዳ ጤናን በተመለከተ የቆዳችን አይነት አውቀን ተገቢ ጥንቃቄ አናድርግ ራሳችንን ከማከም እንድንቆጠብ፡፡ በተቻለ መጠን ከአንዱ ሐኪም ወደ ሌላው አንሂድ በጀመርንበት ቦታ በትዕግስት እንቀጥል፡፡ የቆዳ ብዙ ችግሮች የመመላለስ ባህሪ ስላላቸው ያለብንን ችግር ባህሪ እናጥና ችግራችን ምን እንደሆነ ለማወቅ ከሐኪማችን ጥይቀን እንረዳ፡፡ አንብበን እውቀታችንን እናዳብር፡፡ በተረፈ ቆዳ ትልቅ አካል ነው የተለያየ ችግሮች ሊከሰቱበት ይችላሉ፡፡ ቆዳን የተለየ የሚያደርገው ሁሉ ሰው የሚያየው በመሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ሁሉ ሰው የራሱን አስተያየት ስለ ቆዳ በሽታ ይሰጣል። በመሆኑም ነው ብዙ ስህተቶች የሚፈፀሙት ስለዚህ አንዱ ሰው አሻለኝ ያለውን መጠቀም ማለትም ሌላ ሰው የታዘዘ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ሌላው በመጨረሻ በድጋሚ በማስጠንቀቅ የምፈልገው ባለን ነገር እንርካ እግዚአብሔር የሰጠንን የተፈጥሮ ቆዳ እንቀበል እንውደደው፤ ያልሆነውን ለመሆን አንሞክር ባለን ነገር እንርካ በቆዳችን ብቻ ሳይሆን በሁሉ ነገር ያለንን ነገር ተመስገን ብለን እንቀበል፡፡

I believe that a simple and unassuming manner of life is best for everyone, best both for the body and the mind.

Ruth T

Lorem Ipsum is simply dummy text of the printing and typesetting industry. Lorem Ipsum has been the industry's standard dummy text ever since the 1500s, when an unknown printer took a galley of type and scrambled it to make a type specimen book. It has survived not only five centuries, but also the leap into electronic typesetting, remaining essentially unchanged. It was popularised in the 1960s with the release of Letraset sheets containing Lorem Ipsum passages, and more recently with desktop publishing software like Aldus PageMaker including versions of Lorem.

Social & newsletter

Search