Lifestyle

መጥፎ የአፍ ጠረን

አብዛኞቻችን ደስ የሚል የአፍ ጠረን እንዲኖረን እንፈልጋለን ምክንያቱም መጥፎ የሆነ የአፍ ውስጥ ጠረን በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ያለንን በራስ መተማመን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ በማድረግ ማህበራዊ ግንኙነታችን ላይ ተጽእኖ ያመጣል፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ግንዛቤ ያስጨብጣል ያልነውን አጭር ጽሑፍ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ ተከታተሉት፡-

በምን ምክንያት ይከሠታል

አፋችን ውስጥ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ባክቴሪያዎች አሉ ታዲያ የምንመገበውን ምግብ በአግባቡ ከአፋችን ውስጥ የማናፀዳው ከሆነ ለእነዚህ ባክቴሪያዎች ምቹ የሆነ መራቢያን ፈጠርንላቸው ማለት ነው፡፡ ባክቴሪያዎቹ እነዚህን የምግብ ትርፍራፊዎች በተለይም የኘሮቲንነት (protein) ይዘት ያላቸውን እንዲሠባበሩና ሠልፈር የተባለው ኬሚካል እንዲመነጭ ያደርጋሉ፡፡ የሠልፈር መፈጠር ደግሞ ልክ የበሠበሠ ዕንቁላል አይነት ሽታ በአፋችን ውስጥ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በአፋችን ውስጥ የሚገኘው የምራቅ መጠን ሲቀንስ ለእነዚህ ባክቴሪያዎች ምቹ የመራቢያ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ምክንያቱም ምራቅ በውስጡ ከፍተኛ የሆነ የባክቴሪያዎችን የመራባት ሂደትን የሚገታ ኬሚካል ይይዛል፡፡ በተጨማሪም እነዚህን ባክቴሪያዎች ጨምሮ የተለያዩ ቆሻሻዎችን ከአፍ ውስጥ የማጽዳትን ሚና ይጫወታል፡፡ ጧት ጧት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ከወትሮው የተለየ የአፍ ጠረን የሚኖረን ሌሊት ላይ በአፋችን ውስጥ የሚመነጨው የምራቅ መጠን ትንሽ በመሆኑና ፍሠቱም የተገደበ ስለሆነ ነው፡፡ አብዛኞቻችን ለመጥፎ የአፍ ጠረን ጥርሣችንን በዋና ምክንያትነት የምናቀርብ ሲሆን ነገር ግን ከጥርሣችን በተጨማሪመ ምላሣችን በከፍተኛ ሁኔታ ለዚህ ችግር ዋንኛ ተዋናይ ነው፡፡ በምላሣችን ላይ በሚከማቹ የባክቴሪያዎችና የሞቱ ህዋሣት ግግር ምክንያት ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ይከሠታል፡፡ ከ85-90% የሚሆነው መጥፎ የአፍ ውስጥ ጠረን በዋነኛነት በአፍ ውስጥ በሚከሠት ችግር ምክንያት የሚመጣ ቢሆንም በተወሠነ መልኩ በአፍንጫ ውስጥ በሚጠራቀሙ ቆሻሻዎችና፣ Sinus /ሣይንስ/ በተባለው ህመም ምክንያት መጥፎ ጠረን ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከ 3-5% የሚሆነው ደግሞ ቶኒስል በተባለው ክፍል ላይ በሚከሠት የባክቴሪያና የተለያዩ ቆሻሻዎች ጥርቅም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያሣያሉ፡፡ በጨጓራ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ለመጥፎ የአፍ ጠረን መፈጠር ለምክንያትነት ሊቀርቡ እንደሚችሉ የዘርፍ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

 

ተጨማሪ ምክንያቶች

- በኢንፌክሽን የተጠቃና በውስጡ ፈሣሽ የቋጠረ ጥርስ በተጨማሪም የበሠበሠና የተቦረቦሩ ጥርሶች የችግሩ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

-  የምንመገባቸው ምግቦች ለምሣሌ እንደነጭ ሽንኩርት ያሉት ከሠውነታችን ሙሉ በሙሉ እስኪወገዱ ድረስ መጥፎ የአፍ ጠረንን ይፈጥራሉ፡፡

- የጉሮሮና የሣንባ ኢንፌክሽኖች

- ሠው ሠራሽ ጥርሶችና የተለያዩ በጥርስ ላይ የሚገቡ ተጨማሪ ነገሮች በአግባቡ ጽዳታቸው ካልተጠበቀ ችግሩን ሊያስከትሉ ይችላሉ

- የአንጀት ህመም አልፎ አልፎ ለመጥፎ የአፍ ጠረን መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡

- የጨጓራና የጉሮሮ ካንሠር

- ሲጋራ ማጨስ በሲጋራ ውስጥ የሚገኙት ታር (Tar) እና ኒኮቲን (Nicotine) የተባሉት ጉጂ ኬሚካሎች በምላስ፣ በጥርስና በድድ ላይ በመከማቸት መጥፎ ጠረን እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡

- አልኮል መጠጣት፡- አልኮል የአፍ ውስጥ መድረቅን ለማስከተል ለችግሩ መፈጠር መንስኤ ይሆናል፡፤

- ለተለያዩ ህክምናዎች ተብለው የሚወሠዱ መድኋኒቶችና የካንሠር ህክምና

- በአፍንጫ ከመተንፈስ ይልቅ በተደጋጋሚ ጊዜ በአፍ መተንፈስ

- ለምራቅ አመንጩ ዕጢ ላይ የሚከሠቱ የጤና ችግሮች

- በአፍንጫ ውስጥ የሚጠራቀሙ ቆሻሻዎች

- በምላስና በድድ ላይ የሚኖሩ ማናቸውም ቁስለቶች

- ስር የሠደደ የጉበት ህመም

-ስር የሠደደ የኩላሊት ህመም የመሣሠሉት ናቸው፡፡

- አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠር የአፍ ውስጥ ጠረን በሠውነታችን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ሊከሠት ይችላል፡፡ ለምሣሌ በስኳር በሽተኞች ላይ Fruity odor /የፍራፍሬ/ አይነት ሽታ ሊፈጠር ይችላል ይህም Ketoacidosis /ኬቶአሢዶሲስ/ በተባለው የኬሚካል መፈጠር ሂደት በመሆኑ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡ በተጨማሪም Chronic Kidney Filure /የኩላሊት ስራ ማቆም/ የተጠቁ ሰዎች Ammonia/አሞኒና/ በተባለው ኬሚካል ምክንያት ልክ የሽንት አይነት ሽታ ያለው ትንፋሽ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ታዲያ እንደ እነዚህ አይነት ከተለመደው የአፍ ጠረን ወጣ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ከፍተኛ የሆነ  የህክምና ባለሙያ እርዳታና ክትትል ስለሚያስፈልጋቸው በአፋጣኝ ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት መሄድ ይኖርብናል፡፡

 

ችግሩ መኖሩን እንዴት ማወቅ ይችላል!

- የአንድን ሠው የአፍ ጠረን ጥሩነትና መጥፎነት በቀላሉ መገምገም የምንችለውን ያህል የራሣችንን ግን ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በቅጡ የምናውቅ ብዙዎች ነን አብዛኞቻችን ወደ እጃችን ተንፍሰን በማሽተት ችግሩ የለብንም ብለን ደምድመን ይሆናል ይህ ግን ትክክለኛ ውሣኔ አይደለም ምክንያቱም ስንተነፍስና ስናወራ የምንጠቀመው የአየር አወጣጥ የተለያየ ሲሆን ስንተነፍስ ንፁህ የመሠለን የራሣችን ትንፋሽ ከሌላ ሠው ጋር ስናወራ ለሠውየውም ምቾትን የማይሠጥና መጥፎ ጠረን ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም አፍንጫችን በተደጋጋሚ ጊዜ የለመደውን መጥፎ የአፋችንን ጠረን ችላ ሊለውና ራሣችንን ችግሩ እንደሌላ አድርገን እንድንቆጥር ሊያደርገን ይችላል፡፡ ታዲያ ዋንኛ ችግሩ እንዳለብንና እንደሌለብን ለማወቅ የሚያስችለን ዘዴ በጣም የምንቀርበውን ሠው ስለ አፋችን ጠረን ለመጠየቅና ለመረዳት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማንችል ከሆነ ወደ ጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ጋር ለመቅረብ ችግሩ እንዳለብንና እንደሌለብን ማጣራትና መፍትሔ ማግኘት እንችላለን፡፡ በተጨማሪም የእጃችንን ጀርባ በምላሣችን በመላስና ከደረቀ በኋላ ሽታ እንዳለውና እንደሌለው ለማጣራትና ከምላሣችን ላይ በጥንቃቄ ናሙናዎችን በኘላስቲክና በማይጐዱ ነገሮች ቀርፎ በመውሠድ መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለብን ማጣራት ይቻላል፡፡

image
image

መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ የሚረዱ መፍትኤዎች

- ከእያንዳንዱ ምግብና መጠጥ በኋላ አፋችንን በሚገባ መታጠብና ጥርሣችን በደንብ ማፅዳት ይኖርብናል ከላይ እንዳየነው በየጥርሣችን መሃል በምላሣችን ላይ እንዲሁም በጥርሣችንና በድዳችን መሀል የሚሠገሠገው የምግብ ቅንጣት ለባክቴሪያ መራቢያነት ምቹ በመሆኑ ይህንን አውቀን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ የጥርስ ሣሙናና ብሩሽ የምንጠቀም ከሆነ ጠዋትና ማታ በአግባቡ ጥርሣችንን ማጽዳት ይኖርብናል፡፡ አብዛኛው ሠው ከ1 ደቂቃ ባነሠ ጊዜ ውስጥ ጥርሱን ቦርሾ ሲጨርስ ይስተዋላል ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁሉንም ቆሻሻ ከጥርሣችንና ከአፋችን ውስጥ ለማስወገድ ቢያንስ ለ2 ደቂቃ ያህል በደንብ ማጽዳት ይኖርብናል፡፡ በተጨማሪም የጥርስ ብሩሾቻችንን በደንብ ማጠብና ማጽዳት ከተቻለም ብዙ ጊዜ ሣንጠቀምባቸው መቀያየሩ ጥሩ መፍትሔ ያስገኛል፡፡

- ከጥርሣችን በተጨማሪ ምላሣችን ዋንኛ የባክቴሪያዎች መከማቻ መሆኑን አይተናል ታዲያ ጥርስን ብቻ አሣምሮ አጽድቶ ምላስን መተው እንዲያው ቀልድ ነው፡፡ በመሆኑም ምላሣችንን በማይጐዱና እንዳኘላስቲክ ማንኪያ ያሉትን ነገሮች በመጠቀም /ማንኩያውን ገልብጦ/ በቀላሉ ማጽዳትና በምላስ ላይ የተከማቸውን ግግር ቆሻሻ ማንሣት መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመከላከል የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁላችንም ማወቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ምላሣችንን የምናፀዳው በጣም በጥንቃቄና ምንም አይነት ጉዳትን በማያስከትል መልኩ መሆን ይኖርበታል፡፡

- ፈሣሽ ነገሮችን በተለይም ውኃን አብዝቶ መጠጣት ውኃን በብዛት መጠጣት የአፍ ውስጥ ድርቀትን በመከላከል የምራቅን መጠን ከፍ ስለሚያደርገው ችግሩ እንዳይከሠት ይረዳል፡፡

- ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን አብዝቶ መመገብ ጥሩ የአፍ ጠረንን እንዲኖረን ይረዳል ለምሣሌ ፖም፣ ሙዝ፣ ጥሬካሮት፣ የሎሚ ጭማቂ

- እንደዝንጅብል ያሉ ስራስሮችን አልፎ አልፎ መጠቀሙ ጥሩ የአፍ ጠረንን ይፈጥራል፡፡

- ከስኳር ነፃ የሆኑ (Sugar Free) ማስቲካዎችና ከረሜላዎችን መጠቀሙ የምራቅን መጠን ከፍ ስለሚያደረገው ችግሩን ለመከላከል ይረዳሉ፡፡

- ሲጋራ የምናጨስ ከሆነ ማቆም ይኖርብናል

- የአልኮዎል መጠጥን ፈጽሞ መጠቀም የለብንም፡፡

- ጣፋጭና በውስጣቸው ከፍተኛ የስኳር መጠን ያላቸውን ምግቦችና መጠጦችን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡

- አርቴፊሻል /ሠው ሰራሽ/ ጥርሶች በየቀኑ በአግባቡ መጽዳትና ማታ ማታ በፀረ ባክቴሪያ ኬሚካል ውስጥ መዘፍዘፍ ይኖርባቸዋል፡፡

 

- በጥርሣችን መካከል የሚገኘውን ክፍተት በአግባቡ ማጽዳት ይኖርብናል

- ካፊንን በውስጣዠው የሚይዙ እንደ ቡናና ሻየ የመሣሠሉት የአፍ ውስጥ መድረቅን ስለሚያስከትሉ በተመጠነ ሁኔታ ብቻ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ከእነዚህ ቀላል የቤት ውሰጥ ህክምናዎች በተጨማሪ የተለያዩ ፀረ ባክቴሪያ ሽታን የሚያጠፋ ኬሚካሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በጊዜያዊነት የአፍ ጠረንን የሚያስወግዱ ሲሆን ቋሚና ዘላቅ መፍትሔን ግን አያስገኙም cetyl pyridinium chloride, chlowhexidine, zinc glucordle የመሣሠሉትን ንጥረ ነገሮችን የሚይዙት እነዚህ ኬሚካሎች መጥፎ የአፍ ጠረንን ለማስወገድ በተወሠነ መልኩ አማራጭ መፍትሔዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም H2O2 /ሀይድሮጅን ፐር ኦክሣይድ/ በመጠቀም ለአጭር ጊዜም ቢሆን መጥፎ ጠረንን ማስወገድ ይቻላል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በተለይመ ሀይድሮጅን ፐር ኦክሣይድ በተለያየ የጥንካሬ መጠን ስለሚዘጋጁ ከመጠቀማችን በፊት በውሃ መበረዝና ማዘጋጀት ሊኖርብን ይችላል ይህንንም መረጃ በደንብ ከፊርማሲ ባለሙያው ጠይቆ በመረዳት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በመጨረሻም አንዳንድ የጥርስ ሣሙናዎች በውስጣቸው እነዚህን ከላይ ያየናቸውን የመጉመጥመጫ ኬሚካሎችን በደንብ እንዳየሠሩ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮችን ይይዛሉ ይህም በመሆኑ ሁለቱን ስንጠቀም በተወሠነ መልኩ አራርቀን መሆን ይኖርበታል፡፡

I believe that a simple and unassuming manner of life is best for everyone, best both for the body and the mind.

Albert Einstein

Social & newsletter

Search