Lifestyle

ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን

ይህ የጤና ችግር በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ላይ ሀብታም ደሀ ሳይል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እያጠቃና እየተስፋፋ የሚገኝ ሲሆን እያስከተለ ከሚገኘው የጤና ቀውስ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከፍተኛ እየሆነና አብዛኞቹን የችግሩ ሠለባዎች እየተፈታተነ የመጣ ህመም ነው፡፡

     ይህ ብዙ የተባለለት የጤና ችግር የስርጭት ስነ-ምህዳሩን እያሠፋ በህብረተሰሱ ላይ የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እያሣደረ ይገኛል፡፡ እኛም ይህን ለመገንዘብ ስለአጠቃላይ ችግሩ መጠነኛ ግንዛቤ ለአንባቢያችን ለማስጨበጥ ከዚህ የሚከተለውን መረጃ አቅርበናል ተከታተሉን፡፡

የደም ግፊት ማለት ልባችን ደምን ወደ ተለያዩ ክፍሎች ለማሠራጨት ሲል በደም ቅዳ (Artery) ቧንቧዎች ላይ የሚፈጥረው ግፊት /ጫና/ ሲሆን ይህም ልኬት በ2 ቁጥሮች ይገለፃል፡፡ የላይኛው ልኬት systole /ሲስቶል/ ሲባል የሚፈጠረውም የልብ ጡንቻዎች በሚኮማተሩበትና ደምን በሚረጩበት ጊዜ ነው፡፡ የታችኛው ልኬት ዳይስቶል (Distole) ሲሆን የተኮማተሩበት የልብ ጡንቻዎች ሲለጠጡ የሚፈጠር ግፊት ነው፡፡ በተለምዶ እንደሚታወቀው ጤነኛና ትክክለኛ የግፊት መጠን የሚባለው የግፊት ልኬት መጠን የላይኛው 120mmHG እንዲሁም የታችኛው 80 mmng (120/80) ሲሆን ነው ነገር ግን ይህ መጠን ለተለያዩ ምክንያቶች ሊዛባና ከዚህ ከትክክለኛ የግፊት መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ተከሠተ ለማለት ይቻላል፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የስርጭት አድማሡን እያሠፋ የሚገኝ ሲሆን በመላው ዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ አዋቂ ሠዎች ማለትም ከአጠቃላየ የአለም ህዝብ 26 በመቶ ያህሉ የችግሩ የችግሩ ሠለባዎች ሆነዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ደግመ የስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በሀገረ አሜሪካ በ1995 ዓ.ም እ.ኤ.አ ከነበረበት 43 ሚሊዮን (24%) በ2006 ይህ አሀዝ ወደ 76 ሚሊዮን (34%) እንደጨመረ የተለያዩ ጥናቶች አመላከተዋል፡፡ እነዚሁ ጥናቶች አያይዘውም እንደገለፁት በአደጉት ሀገራት ከ350 ሚሊዮን በላይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ደግመ ከ650 ሚሊዮን በላይ የችግሩ ሠለባዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ በዚህ ህመም ዙሪያ የሚሠሩ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች እንዲሁም የጥናትና ምርምር ተቋማት የደምልኬት መጠንን ለመከፋፈል ትክክለኛውንና ከፍተኛውን የግፊት መጠን ለመለያዩ ለማወቅ የሚያስችሉ ደረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ የክፍፍል መስፈርቶች ለአብዛኛው ህዝብ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ነገር ግን በተለያዩ የጤና ችግሮች ምክንያት ከዚህ የልኬት ክፍፍል ውጪ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

 

 

 

የላይኛው የደም ግፊት መጠን

(Systolic pressure)

 (mmhg)

የታችኛው የደም ግፊት መጠን

(Diastolic pressure)

 (mmhg)

1. ትክክለኛው የደም ግፊት መጠን

ከ90-119

ከ60-79

2. ቅድመ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን

ከ120-139

ከ80-89

3. የመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን

ከ140-159

ከ90-99

4. ሁለኛ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን

ከ160 በላይ

ከ100 በላይ

   

     ከእነዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የላይኛው የልኬት መጠን ከፍተኛ ሊሆንና የታችኛው ደግሞ በትክክለኛው መጠን ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህ የደም ግፊት ልኬት ሰንጠረዥ እንደሚያሣየው በቅድመ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የተለያዩ በጤና ባለሙያዎች የሚነገሯቸውን የደም ግፊት መቆጣጠሪያ ምክሮችን ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ በጊዜ ሂደት ወደ መጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን የመሸጋገር ዕድላቸው ሠፊ ነው፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ዓይነቶች

የደም ግፊት ዓይነቶት በዋነኛነት የመጀመሪያ (primary) እና ሁለተኛው (secondary) በመባል ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያ (Primary) የሚባሉት እስካሁን ድረስ በግልጽ መነሻ ምከንየታቸው እነዚህ ናቸው ለማለተ የሚያስችል መረጃ ያልተገኘላቸውና ምክንያታቸውም ይሄ ነው ብሎ ነቆሶ ለማውጣት አስቸጋሪ የሆኑት ሲሆን ከ90-95% የሚሆኑት ለከፍተኛ የደም ግፊት መጠን የተጠቁ ሠዎች በዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ እነዚህ የመጀመሪያ (primary) ከፍተኛ የደም ግፊቶች አንድ መንስኤ የሌላቸው ሲሆን በተለያዩ መንስኤዎች መስተጋብር ምክንያት ይፈጠራሉ በተለይም ከGene /ዘረ-መል/ ጋር ተያይዘው የሚከሠቱ ለውጦች እንደምክንያትነት ይቀርባሉ ነገር ግን በተጨባጭ የትኛው ዘረ-መል ችግሩን ያስከትላል የሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም፡፡ በቅርቡ የተለያዩ ጥናቶች በእነዚህ ዘረ-መሎች ላይ እየተደረጉ ሲሆን በተለይም R-A-A የተባለውን ሲስተም የሚቆጣጠሩ ዘረ-መሎች ላይ ሰፊ ጥናት እየተደረገ ነው ይህ R-A-A (Renin Angiotensin Aldosterone) ሲስተም የጨውን መጠንና የደም ቧንቧዎችን መኮማተር በመቆጣጠር የደም ግፊት መጠንን በሠውነታችን ውስጥ የሚያስተከክል ተፈጥሮአዊ ዘዴ ነው፡፡

     ሁለተኛው የደም ግፊት ዓይነት Secondary /ሁለተኛ/ የሚባለው ሲሆን ይህ ከፍተኛ የደም ግፊት አየነት በምን ምክንያት እንደተከሠተ መንስኤዎቹ በግልፅ የሚታወቁና እነዚህ እነዚህ ናቸው ተብለው መገለፅ የሚችሉ ናቸው ይህ አይነቱ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ከ5-10% የሚሆኑትን ህሙማን ያጠቃል እነዚህን የሚታወቁ መንስኤዎች ለመቆጣጠርም ከፍተኛ የደም ግፊት መጠኑን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከመንስኤዎቹም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • በኩላሊትና በአካባቢው በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሠት የጤና ችግር ለከፍተኛ የደም ግፊት መፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም የተጠራን ደም ለኩላሊታችን የሚያደርሠው የደም ቧንቧ በተያዩ ምክንያቶች ከጠበበ /በስብ ግግር ሊሆን ይችላል/ ወደ ኩላሊታችን የሚደርሠው የደም መጠን ይቀንሣል በዚህም ምክንያት ኩላሊታችን (Renin) ሬኒን የተባለውን ኬሚካል ሆርሞን ያመርተል ይህ ኬሚካልም ሌላ ኢንጂዎቴንሲን (Angiotensin) ከተባለ ሆርሞን ጋር በመሆን የተለያዩ የደም ቧንቧዎችን ሊያኮማትሩና በውጤቱም የደም ግፊት መጠንን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
 • ከፍተኛ የሠውነት ክብደት መጠን1- በከፍተኛ ውፍረት ምክንየት አላስፈላጊ የስብ ክምችት ይኖራል፡፡ ለዚህ ትርፍ አካል ደም ለማዳረስ ሲል ልባችን ከወትሮውና ከትክክለኛው መጠን በተለየ የስራ ጫና ይኖርበታል ይህም ለደም ግፊት መጨመር ምክንያት ሊሆን ይችላል ይህ ከልክ ያለፈ ውፍረት የኢንሱሉን መቋቋም (Resistance) ሊፈጥር ይችላል፣ የተለያዩ ጐጂ የስብ ዓይነቶች በደም ስሮች ውስጥ እንዲጠራቀም ያደርጋል በአጠቃላይ የመጨረሻ ውጤቱ የግፊት መጠን መጨመር ይሆናል፡፡ እነዚህ በከፍተኛ የክብደት ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በመኝታ ወቅተ በሚፈጠር መታፈን ምክንያት በተደጋጋሚ ለኦክሲጅን እጥረት ስለሚጋለጡ የአድርናል ዕጢ ሆርሞኖችን ሊያመነጭና የደም ግፊት መጠን ሊጨምርባቸው ይችላል፡፡

በአሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት ዕድሜያቸው ከ20-45 ዓመት ያሉ ከፍተኛ የሠውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ከ5-6 እጥፍ በከፍተኛ የደም ግፊት የመጋለጥ እድል እንዳላቸው ጠቁሟል፡፡

 • የስኳር ህመም .. ለዚህ ህመም ምክንየት በተለያዩ የደም ስሮች ላይ የሚደርሱ ጉዳዮች ችግሩን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
 • ሠውነታችን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በአግባቡ ለመውጣት የተለያዩ ሆርሞኖችን ያመርታል ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የእነዚ ሆርሞኖች መጠን ከተገቢው መጠን መጨመር ከፍተኛ የደም ግፊት ያስከትላል ለምሣሌ የአልደስትሮን (Aldosterone) እና የፖራታይሮይድ (parathyroid) ሆርሞን መጠን መጨመር
 • Pheochuomocytomd /ፊዋክሮምሣይቶማ/ የተባለውና የነርቭ ህዋሣትን ግንኙነት የሚያቀላጥፍ ኬሚካሎችን ለከፍተኛ መጠን የሚያመርት ዕጢ በሠውነት ውስጥ መፈጠር
 • እርግዝና … በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል
 • የታይሮይድ ዕጢ ላይ በሚከሠቱ ችግሮች ምክንያት የሚያመርተው የሆርሞን መጠን ሲዛባ ከፍተኛ የደም ግፊት ይከሠታል
 • ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮሆል በየቀኑ መጠጣት እንዲሁም ሲጋራ ማጨስ የደም ግፊት መጠንን ይጨምራሉ በተጨማሪም ከእነዚህ ሱስ ተጠቃሚው እናቶች የሚወለዱ ህፃናት ወደፊት ለከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ሊጋለጡ እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ በተጨማሪም የእናት ጡት ወተትን በአግባቡ አለማግኘትም ከችግሩ ጋር ሊያያዝ ይችላል
 • በተለያዩ ደም አስተላላፊ ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር የስብ ክምችትና የተለያዩ አደጋዎች
 • ለተለያዩ ህመም ህክምና ተብለው የሚወሠዱ መድኃኒቶች የደም ግፊት መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ በተለይም ስቶሮይድስ(steroids)
 • የተከላከሉና አደገኛ ዕፆች ችግሩን ያስከትላሉ ለምሣሌ Cocaine (ከኬይን) እና Amphetamine አምፊታሚን ይገኝበታል
 • ከፍተኛ መጠን ያለው ጨው መጠቀም
 • አንዳንድ ጊዜ በዘር ሀረግ ውስጥ የችግሩ ሠለባ ካለ ከሌላው በተለየ መልኩ በስፋት ሊከሠት ይችላል አፍሪካ አሜሪካዊ ዝርያ ያላቸው ሠዎች ለከፍተኛ የደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
 • የአድሬናል ዕጢ ላይ የሚከሠቱ የተለያዩ የጤና ችግሮች
 • አንዳንድ የባህላዊ ህክምና ቅጠላ ቅጠሎችና ስራ ስሮች የደም ግፊት መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡

የከፍተኛ ደም ግፊት ምልክቶች

 • ከፍተኛ የደም ግፊት በአብዛኛው ጊዜ ምልክቶችን የሚያሣይ ሲሆን ህሙማኑ ለሌላ የጤና ችግር ወደ ጤና ተቋማት ሲሄድ በአጋጣሚ ምርመራ የሚገኝ የህመም ዓይነት ነው አብዛኛው ህሙማን ችግሩ እንዲለበት ለረጅም ጊዜ ስለማያውቅ ህመሙ ቀስ በቀስ ስር እየሰደደ ተያያዥ የጤና ችግሮችን ማስከተሉ አይቀርም አንዳንድ ጊዜ የግፊት መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን አንዳንድ ተያያዥ ምልክቶች መከሰታቸው አይቀርም ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
 • በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሠቱ ከባድ የራስ ምታት በተለይም ስሜቱ በኋለኛው የጭንቅላት ክፍልና ማጅራት አካባቢ ሊሆን ይችላል ስሜቱ ጠዋት ጠዋት ከባድ ሊሆን ይችላል
 • ድንዝዝ የማለት ስሜት
 • በእይታ ላይ የሚፈጠሩ አንዳንድ መዛባቶች ብዥ የማለት ሁኔታ ሊኖር ይችላል
 • ማቅለሽለሽና ማስመለስ
 • ተደጋጋሚ ነስር
 • የማዘር ስሜት፣ ማጥወልወል
 • ጆሮ አካባቢ የተለያዩና የሌሉ ድምፆች ሊፈጠሩና ሊሠማን ይችላል
 • የግፊት መጠኑ በጣም ከፍተኛ እየሆነ ሲመጣ
 • በደረት አካባቢ ከፍተኛ ህመም
 • ለመተንፈስ መቸገር
 • የልብ ምት መቸገር
 • በተደጋጋሚ ራስን መሣት
 • ደም የተቀላቀለበት ሽንት
 • የአስተሣሰብ መዛባትና የመደናገር ስሜት
 • የመሣሰሉት ሁኔታዎች ይከሠታል

እነዚህ ከላይ ያየናቸው የህመሙ ምልክቶች አልፎ አልፎ የሚከሠቱና ጥቂት በሚባሉ ህሙማን ላይ የሚኖሩ ናቸው እነዚህ ምልክቶች አልታዩም ማለት ከፍተኛ የደም ግፊት ችግር የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ህመሙ በአጠቃላይ የተለያዩ ምልክቶችን የማያሣይና ውስጥ ውስጡን የሚጐዳ በመሆኑ በየጊዜው ወቅቱን የጠበቀ ምርመራ ማድረግና የጤንነት ሁኔታን መከታተል ያስፈልጋል፡፡

ስር የሠደደ ከፍተኛ የደም ግፊት

 • ከላይ ለመግለፅ እንተሞከረው ከፍተኛ የደም ግፊት ውስጥ ውስጡን ስር እየሠደደ በተለያዩ የሠውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን ያስከትላል ህመሙ በአብዛኛው ምልክቶችን ስለማያሣይ ህመምተኛው ይህ ችግር እንዳለበት አይረዳም፡፡ ከ30-50 በመቶ የሚሆኑት ህሙማን ከ8-10 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ አካል ጉዳቶች ሊዳረጉ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሣያሉ፡፡ የችግሩ ስር መስደድ የሚከተሉትን አደገኛ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል
 • ከትልቁ ደም ቅዲ ቧንቧ (Aorts) እና የተለያዩ ሆድና እግር አካባቢ ደምን ከሚያሠራው የደም ቧንቧዎችና ስሮች በኩል የደም መፍሠስ ሊኖር ይችላል፡፡
 • ለከፍተኛው የደም ግፊት ምክንያት ስር የሠደደ የኩላሊት በሽታ ሊከሠት ይችላል
 • የተለያዩ ዓይነት የልብ ህመሞች ብሎም በአጠቃላይ በከፍተኛ ሁኔታ የልብ ስራ መስተጓጐል
 • ወደ ተለያዩ የሠውነት ክፍል የሚሄደው የደም ፍሠት መጠን መቀነስ
 • ወደ አንጐል ውስጥ የደም መፍሠስና ተያያዥ የጤና ችግሮች (Stroke)
 • የአይን የተለያዩ ክፍሎች መጐዳትና የእይታ መስተጓጐል
 • የተለያዩ የደም ስሮች መጐዳትና መጥበብ
 • በሣምባ ላይ የፈሣሽ መቋጠርና መጠራቀም
 • የአዕምሮ በአግባቡ መስራት አለመቻልና የማሠብ ችሎት መቀነስ የመሣሠሉት ሁኔታዎች ይከሠታሉ አንዳንድ ጊዜ የደም ግፊት መጠኑ ከ180 በ110 በላይ ሊሆን ይችላል ይህም ለህመምተኛው ኢስኒ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን በቶሎ እርምጃ ካልተወሰደ የሚከሠተው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡

የተለያዩ ምርመራዎች

አብዛኛው ህሙማን ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዳለበት የሚታወቀው በአጋጣሚ ለሌላ ህመም ህክምና ወደጤና ተቋማት ሲሄድ ነው፡፡ ይህንን የጤና ችግር መኖሩን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው ዘዴ በቀጥታ የህመምተኛውን የደም ግፊት መጠን መለካት ነው ይህ ልኬት በተደጋጋሚ መደረግ ያለበት ሲሆን ተመሣሣይ ውጤት ከተገኘ ችግር እንደተከሰተ አመላካች ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ልኬት ከፍተኛ የደም ግፊት አለ ብሎ መወሠን አይቻልም በተደጋጋሚ መከናወን አለበት አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሮአቸው ወደ ህክምና ተቋማት ሲመጡና ነጭ ጋወን የለበሰ የጤና ባለሙያ ሲያዩ የመረበሽና በድንጋጤ የመፍራት ሁኔታ ይኖራቸዋል ይህም በራሱ የደም ግፊት መጠናቸው እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል ይህንንም ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ልኬቱ መከናወን ይኖርበታል አንዳንድ ባለሙያዎች ሆስፒታል ከሚደረጉ የደም ግፊት ልኬቶች በተሻለ በመኖሪያ ቤት የሚደረገው ትክክለኛ ውጤት እንደሚሠጥ ይጠቁማሉ ምክንያቱም ህመምተኛው በቤቱ ዘና ባለ ስሜት ሣይጨናነቅ ሆኖ የሚካሄደው ልኬት ትክክለኛ መረጃን በመስጠት በኩል ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ የደም ግፊት ልኬት በተጨማሪ ባጠቃላይ ለህሙማኑ የተለያዩ ምርመራዎች የሚደረጉለት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ

 • በኩላሊት ላይ የተከሠተ የጤና ችግር መኖሩን ለማወቅ የተለያዩ የሽንት ምርመራዎች በተለይም የኘሮቲን መጠንን ለማወቅ፣ Serum Buns የደም ውስጥ የሪያ እና ናይትሮጅን የኬራቲኒን (creatinie) መጠን፣ GFR የኩላሊትን የማጣራት አቅም ለማወቅ
 • በደም ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኤሌክትሮላይቶችን በተለይም የሶዲየም (Sodium) potassium ፓታሺየም እና ካልሲየም (calcium) የመሣሠሉት
 • የትይሮይድ ቀስቃሽ ሆርሞን (TSH) መጠን ምርመራ
 • የደም ውስጥ ግሉኮስ (Glucose) መጠን
 • አጠቃላይ የኮሌስትሮል (Cholestrol), HDL እና LDL እንዲሁም የትራይልላይሠራድድ መጠን
 • በልብ ላይ የደረሠውን የጤና ችግር ለማወቅ የኤኮካርዲዮግራም (Echocardiogram) እና (electrocardiogram) ምርመራዎች
 • በዓይን ላይ የተከሠተውን ችግር ለማወቅ በተለይም (refinopathy) ሬቲናፖቲ መከሠቱን ለማወቅ የተለያዩ የዓይን ምርመራዎች
 • የደረት x-ray /ኤክስሬይ/ የልብ መጠን መጨመርና ተያያዥ ጉዳቶችን ለማወቅ ያስችላል
image
image

የከፍተኛ የደም ግፊት ህክምናና መከላከያ መንገዶች

 • ከፍተኛ የደም ግፊት መጠንን አስቀድሞ እንዳይከሠት ለመከላከል የሚረዱ የተለያየ አማራጭ መንገዶች ያሉ ሲሆን እነዚህን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ችግሩ ሣይከሠት ለመከላከልና ትያይዘው ከሚመጡ የተለያዩ አደጋዎች ለመጠበቅ ያስችላል፡፡

እነዚህ የደም ግፊት መጠን መጨመርን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. በየጊዜው ተከታታይነት ያለው እስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ

በሣምንቱ አብዛኛው ቀናት ውስጥ ከ30-60 ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ እስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የደም ግፊት መጠንን ከ4-9 mmhg ያህል ለመቀነስ ያስችላል የግፊት መጠኑን ለውጥ ለማምጣት ረጅም ጊዜ የማይረጅ ሲሆን እስፖርቱን በጀመርን በጥቂት ሣምንታታ ውስጥ የደም ግፊት መጠናችን ይቀንሣል በቅድመ ከፍተኛ ግፊት መጠን ክልል ውስጥ ማለትም የላይኛው ከ120-139 የታችኛው ደግሞ ከ80-89 mmhg ክልል ውስጥ የምንገኝ ከሆነ እስፖርት መስራቱ ወደ ከፍተኛው የደም ግፊት መጠን ምድብ ውስጥ እንዳንገባ ይረዳናል፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችን በማማከር የእስፖርታዊ እንቅስቃሴዎቹን አይነትና ኘሮግራም ማውጣት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከልብ ጋር በተያያዘ የጤና ባለሙያዉ ጋር በደምብ መመካከርና መወያየት ይኖርብናል በተጨማሪም ሣምንቱን ሙሉ ያልሠራነውን እስፖርት ለማካካስ ብለን ባንድ ጊዜ ደራርበን ከባባድ እስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ዋና፣ ብስክሌት መንዳት፣ ሶምሶማ ሩጫና ረዘም ያሉ ወኮችን ማድረጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

 1. የአመጋገብ ጥንቃቄ ማድረግ

የቅባትና የስብ መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዲከሠት በር ከፋች መንገድ ነው፡፡ የሣቺሬትድ ስብ (saturated fat) እና ኮሌስትሮል (cholesterol) መጠንን ቀንሶ መጠቀም የደም ግፊት መጠንን እስከ 14 mmhg ለመቀነስ እንደሚያስችል ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ በአመጋገባችን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም ጥራጥሬዎችን ማዘውተሩ ለጤነነት በጣም ጠቃሚ ነው በፖተሲየም (potassium) ይዘታቸው የበለፀጉ እንደ ሙዝ ሐብሐብ፣ ብርቱካን፣ ቆስጣ፣ ዝኩኒ የመሣሠሉትን ምግቦችን መጠቀም የደም ግፊት መጠንን በትክክለኛው መጠን ውስጥ ለመጠበቅ እንደሚያስችል ይታመናል በአሠር የበለፀጉ ምግባችን በማዘውተር ውሃ በብዛት በመጠጣት ይህንን የጤና ችግር በአግባቡ ለመቆጣጠር አማራጭ መንገዶች ናቸው፡፡

 1. የምንወስደውን የጨው መጠን መመጠን

የምንወስደውን የጨው መጠን መመጠን ከ2-8 mmhg የሚደርስ የደም ግፊት መጠንን ለመቀነስ እንደሚያስችል ይታወቃል በየቀኑ ከ2.3 ግራም በታች ሶዲየም መጠቀም ያለብን ሲሆን ይህም ከ1 ሻይ ማንኪያ በታች ማለት ነው፡፡ ይህ መጠን ደግሞ የደም ግፊታቸው ከፍተኛ የሆነ እንደሁም ዕድሜያቸው ከ57 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ደግመ ከ1.5 ግራም በታች ማለትም ግማሽ የሻይ ማንኪያ ወይም ከዛ በታች ብቻ ጨው መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ የታሸጉ ምግቦችን የምንጠቀም ከሆነ በደንብ በማሸጊያቸው ከፍተኛ የጨው መጠን አላቸው እነዚህን ምግቦች በምናበስልበት ጊዜ የምንጠቀመውን የጨው መጠን መቀነስ ወይም መተው አለብን፡፡ በአንድ ጊዜ የጨው መጠንን መቀነስ የለመድነው ጣዕም ሊያሣጣንና ላይመቸን ይችላል፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ቀስ በቀስ በትንሽ በትንሽ እያደረግን ብንሔድ ልንለምደውና ላያስቸግረው ስለሚችል የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

 1. የአልኮሆል መጠንን መቀነስ

አልኮሆልን አብዝቶና አዘውትሮ መጠጣት የተለያዩ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንዳሣዩት ወንዶች በየቀኑ የተጣራ 30ml አልኮሆል ሴቶች ደግሞ 15ml እና ከዛ በላይ የሚጠጡ ከሆኑ ለከፍተኛ የደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ከዚህም ያነሠ መጠን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ወንዶች ከ2 ጠርሙስ ቢራ ወየም ከ300ml ወይም ከ60ml የተጣራ ውስኪ ሴቶችና ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ደግመ ከዚህ በግማሽ ያነሰ መጠን በላይ በየቀኑ የሚወስዱ ከሆነ ለከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንደሚጋለጡ በየጊዜው የሚወጡ የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ፡፡ አልኮልን ከተገለፀው መጠን በላይ በከፍተኛ ሁኔታ በየቀኑ የምንጠቀም ከሆነ ቀስ በቀስ መቀነስና ማቆም ይኖርብናል በተለይም የተለያዩ የደም ግፊት መጠንን የሚያስተካክሉ መድኃኒቶተን የምንወስድ ከሆነ በፍፁም አልኮል መጠጣት የለብንም፡፡

 1. ሲጋራ አለማጨስ

በምናጨስበት ጊዜ በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን የደም ግፊት መጠንን እስከ 10mmhg በሚደርስ መጠን ከፍ ያደርገዋል ይህም ማለት በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የምናጨስ ከሆነ የደም ግፊት መጠናችን ከፍተኛ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በተለይም ደግመ የደም ግፊታቸው ከፍተኛ ሆኖ በዛ ላይ ሲጃራ የሚያጨሱ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም ባናጨስም እንኳን ሌሎች ሲያጨሱ የሚወጣው ጭስ ለጉዳት ሊዳርገን ይችላል ስለሆነም ይህንንም መጠንቀቅና መከላከል ይኖርብናል፡፡

 1. ቡና እና ሌሎች ካፈን የሚይዙ መጠጦችን መቀነስ

ቡናን አዘውትሮ መጠጣት የደም ግፊት መጠንን ከፍ ያደርጋል ብሎ ለመወሠን የሚያስችል ጥናት እስካሁን አልተገኘም የተለያዩ ጥናቶች ቡና ላይ የተለያየ አመለካከትና ውጤት እንደሚያስብትል አሣይተዋል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ያላቸው ሠዎች ቡናን አዘውትረው መጠቀም እንደሌለባቸው የጤና ባለሙያዎች ያሣስባሉ፡፡ ቡና በተጠጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጊዜያዊ የደም ግፊት መጠን መጨመርን ያስከትላል ነገር ግን ይህ የመጠን መጨመር ጊዜያዊ ይሁን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በትክክል የሚያሣይ መረጃዎች የሉም በተጨማሪም በስኳር የበለፀጉ የለስበሣና አንዳንድ የኢነርጂ መጠጦችም በተመሣሣይ በውስጣዠው ካፊስ ሲለማይዙ የደም ግፊትን የመጨመር ኃይል አላቸው፡፡

 1. ከፍተኛ የሠውነት ክብደት መጠንን መቀነስ

የደም ግፊት መጠን ከሠውነት ክብደት መጨመር ጋር ተያይዞ ይጨምራል በመሆኑም ከፍተኛ የሠውነት ክብደት መጠንን መቀነስ የደም ግፊት መጠኑም እንዲቀንስ ይረዳል 10 ኪ.ግ ያህል ክብደት መቀነስ የደም ግፊት ከ5-20 በሚደርሰ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በወገብ አካባቢ ከፍተኛ የስብ ክምችት መኖር ለዚህ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን እንዴት ወደ ትክክለኛው የክብደት ክልል መምጣት እንደምንችል መመካከርና የተለያዩ የአመጋገብ ስርዓቶችንና እስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ ውጤቱ ከፍተኛና ጠቃሚ ነው፡፡

 1. ጭንቀትና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ማስወገድ

ጭንቀት የደም ግፊት መጠን በጊዜያዊነት እንደሚጨምር ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ለዚህ ችግር የሚያጋልጡን ምክንያቶች ለይቶ በማወቅ ከተቻለ ማስወገድ ካልሆነም ሣንጨናነቅ በአግባቡ እነዚህን ነገሮች ለማለፍ መሞከር ያስፈልጋል ነገር ግን ነገሮች ከአቅማችን በላይ ከሆኑ የስነልቦና ጤና ባለሙያዎችን ማማከርና የተለያዩ ዕርዳታዎችን ማግኘት እንችላለነ፡፡

 1. የቤተሰብና የጓደኛን እርዳታ ማግኘት

እነዚህ አካላት የተለያዩ እገዛዎችን ለማድረግ ጤንነታችንን እንድንከባከብና እንደንቆጣጠር ያስችሉናል የተለያዩ እስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለብቻ ከማድረግ ይልቅ ከተለያዩ ሠዎች ጋር ማድረጉ የበለጠ በሞራል እንድንቀሣቀስና እንዳናቋርጠው ለማድረግ ይረዳናል፡፡

በመጨረሻም በየጊዜው ተከታታይነት ዓለው የደም ግፊት መጠን ልኬት ማድረግ ችግሩ ከመከሠቱ በፊት ለመቆጣጠርና ተያያዥ የጤና ችግሮች እንዳይከሠቱ ለማድረግ የጐላ ሚናን ስለሚጫወት በተቻለ አቅም ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ውድ አንባብያን በሚቀጥለው እትማችን ስለተለያዩ የደም ግፊት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ ህክምናዎች ይዘንላችሁ እንደምንቀርብ ቃል በመግባት ለዛሬው በዚሁ አበቃን፡፡

I believe that a simple and unassuming manner of life is best for everyone, best both for the body and the mind.

Albert Einstein

Lorem Ipsum is simply dummy text of the printing and typesetting industry. Lorem Ipsum has been the industry's standard dummy text ever since the 1500s, when an unknown printer took a galley of type and scrambled it to make a type specimen book. It has survived not only five centuries, but also the leap into electronic typesetting, remaining essentially unchanged. It was popularised in the 1960s with the release of Letraset sheets containing Lorem Ipsum passages, and more recently with desktop publishing software like Aldus PageMaker including versions of Lorem.

Social & newsletter

Search