Medical

ትርፍ አንጀት | ለትርፍ አንጀት መከሠት መንስኤዎች | what's appendicitis

አፔንዲሳይቲስ ወይም በተለምዶ ትርፍ አንጀት በመባል የሚታወቀው ህመም የሚከሰተው  አፔንዲክስ በተባለው የሠውነት ክፍል ላይ በሚፈጠር መቆጣት ምክንያት ነው፡፡ በአሜሪካ ከ6.7-8.6 በመቶ የሚሆኑትን የህብረተሰብ ክፍል ያጠቃል በየዓመቱም እስከ 250000 የሚደርሱ ሠዎች በዚህ ችግር ይጠቃሉ:: ይህ በሽታ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሠዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም በታዳጊዎችና በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን በስፋት ያጠቃል፡፡ አፔንዲክስ የሚገኘው በትልቁ አንጀታችን የመጀመሪያ ክፍል ላይ ሲሆን ልክ የጣት አይነት ቅርፅ ሲኖረው በተለያዩ ሠዎች ላይ የተለያየ መጠንና የአቀማመጥ ሁኔታ ይዞ ይታያል፡፡ አፔንዲክስ ውስጡ ክፍትና ከትልቁ አንጀት ጋር የሚገናኝ ቀዳዳ ሲኖረው ይህ የአፔንዲክስ ውስጣዊ ግድግዳ ትንሽ መጠን ያለው ወፍራም ፈሣሽ ያመነጫል፤ ይህም ፈሳሽ ወደ ትልቁ አንጀት ይፈሣል፡፡ የተለያዩ ጥናቶች ቢደረጉም የአፔንዲክስን ጥቅም ግን ይህ ነው ለማለት የሚያስችሉ ግኝቶች አልተገኙም፡፡ ነገር ግን በተወሠነ መልኩ በሽታ ተከላካይ ህዋሣትን ሊያመነጭ እንደሚችሉ የሚያሣዩ መረጃዎች አሁን አሁን ብቅ እያሉ ነው፡፡

 

ለትርፍ አንጀት መከሠት መንስኤዎች

- ከላይ እንዳየነው በአፔንዲክስና በትልቁ አንጀት መካከል ቀዳዳ ወይም ክፍተት አለ ታዲያ ይህ ቀዳዳ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘጋና አፔንዲሣይቲስ /ትርፍ አንጀት/ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከእነዚህም ምክንያቶች ውስጥ፡-

 • ከውጭ ወደ ሠውነታችን የገቡ ባዕድ ነገሮች
 • በአንጀት ውስጥ የሚገኙ ትላትሎች
 • ወደ ካልሲየምነት የተቀየረና በጣም ጠጣር የሆነ የሠገራ ክምችት
 • በአፔንዲክስ ውስጥ የሚገኘው Lymphatic tissue (ሌፋቲክ ቲሹ) በተለያዩ ምክንያቶች ሲያብጡ ለምሣሌ ኢንፌክሽኖች በሚፈጠሩ ጊዜ
 • በአንጀትና በአፔንዲክስ ላይ የሚፈጠሩ የካንሰር ዕጢዎች (Cancer) የመሣሠሉት ናቸው፡፡
 • በአካባቢው ላይ የተከሠቱ የተለያዩ አደጋዎች
image
image

በእነዚህና በሌሎች የተለየዩ ምክንያቶች ይህ በአፒንዲክስና በትልቁ አንጀት መካከል ያለው ቀዳዳ ሲዘጋ በአፒንዲክስ ውስጥ የሚመነጨው ወፍራም ፊሣሽ ወደ ትልቁ አንጀት መፍሠሡን ያቆምና እዛው አፔንዴክስ ውስጥ እየተከማቸ ይመጣል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሚከተሉት ሁኔታዎች ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡

 1. የመጀመሪያው ደረጃ፡- በአፔንዲክሱ መዘጋትና ፈሣሽ መጠራቀም ምክንያት አፔንዴክሱ እንዲያብጥና ቁስለት እንዲፈጠርበት ከማደርረግ ባለፈ የተለያዩ የባክቴሪያ አይነቶችም አካባቢውን መውረር ይጀምራሉ፡፡ የአፔንዲክሱ እብጠት እየጨመረ ሲመጣ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ግፊት ይፈጠራል በዚህም በአካባቢ የሚገኙ ነርቮች ስለሚነቃቁ በሽተኛው መጠነኛ የሆነ እምብርት አካባቢ የህመም ስሜት ይኖረዋል፡፡ ይህ ህመም አብዛኛውን ጊዜ ከ4-6 ሠዓቶችን ሊወስድ ይችላል፡፡
 2. በመቀጠል በአፔንዲክስ ላይ ያለው ከፍተኛ ግፊት እየጨመረ ሲመጣ በአካባቢው ያለውን የደም ዝውውር ያስተጓጉለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ባክቴሪያዎች የአፔንዲክሱን ግድግዳ በስፋት ወረው ይይዛሉ፡፡ ሠውነታችንም ታዲያ ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያመነጫቸው በሽታ ተከላካይ ህዋሣት የአፔንዲክሱን ግድግዳ ከጥቃት ለመከላከል በሚወስዱት እርምጃ ምክንያት የግድግው መቆጣት እየተባባሠ ይመጣል፤ ይህ በኢንፌክሽን የተበከለው የአፔንዲክስ ግድግዳ ከሆድ ዕቃ ግድግዳ ጋር ስለሚገናኝ ኢንፎክሽኑ ወደ ሆድ ዕቃ ግድግዳ ይተላለፋል፡፡ በዚህም ምክንያት የህመሙ ስሜት በታችኛው የቀኝ ሆድ ክፍል ላይ ይሆናል ይህ የህመም ስሜት ተከታታይነት ያለውና መጀመሪያ ከነበረው የህመም ስሜት የከፋ ነው፡፡
 3. በአካባቢው ያለው የደም ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጐለ ሲመጣ ጋንግሪን (Gangrene) ይፈጠራል፡፡ ይህም ማለት በቂ ንጥረ ነገርና ኦክሲጅን በደም በኩል ሲያገኝ የነበረው የአፔንዲክስ ግድግዳ የደም ዝውውሩ ሲቋረጥበት እነዚህን ጠቃሚ ነገሮች ያጣል በዚህም ህዋሣቱ መሞት ይጀምራሉ፡፡
 4. ይህ የአፔንዴክስ ግድግዳ ህዋሣት እየሞቱ መሄድ ግድግዳው እንዲበሣና ያበጠው አፔንዴክስ እንዲፈርጥ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ የአፔንዴክስ መፍረጥ በውስጡ የነበረው በባክቴሪያ የተበከሉ ፈሣሽ ወደ አካባቢው እንዲሠራጭ ያደርገዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የሆድ ዕቃ ግዳግዳን (peritoneum) ሊበክለውና ከፍተኛ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ባክቴሪያዎች ወደ ደም ውስጥ ለመግባትና ወደ ተለያዩ የሠውነት ክፍሎች በመሄድ ለህይወት አስጊ የሆነ ኢንፌክሽኖችን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ የአፔንዲክስ መዘጋት የአንጀትን ጡንቻዎች በአግባቡ እንዳይሠሩ ሊያደርግ ይችላል በዚህም በአንጀት ውስጥ የምግብና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች መተላለፍ ሊስተጓጐል ይችላል ታዲያ ከተዘጋው በላይ ያለው የአንጀት ክፍል በፈሣሽና በጋዝ መሞላት ሲጀምር በከፍተኛ መጠን የሆድ ማበጥ ይከሠታል፡፡ ማቅለሸለሽና ማስመለስ ይኖራል፡፡

 

የህመሙ ምልክቶች

      

የትርፍ አንጀት ህመም በተለየዩ ሠዎች ላይ የተለያዩ ምልክቶችን የሚያሣይ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ምልክቶቹ ለመታየት ከ4-48 ሠዓት ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡

- እንብርት አካባቢ ቀስ ብሎ የሚጀምር የህመም ስሜት ይኖራል ይህ የህመም ስሜት ቀስ በቀስ እየጨመረ ይመጣና ወታችናው ቀኝ የሆድ ክፍል አካባቢ ይሠማል እንዲህ አይነቱ የህመም ስሜት ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ህመምተኞች ላይ ይታያል፡፡

- ከ74-78 በመቶ የሚሆኑት የትርፍ አንጀት ህመምተኞች ከፍተኛ የሆነ የምግብ ፍላጐት መቀነስ ይኖርባቸዋል፡፡

- ማቅለሽለሽና ማስመለስ በአብዛኞቹ ላይ ይታያል፡፡

- የሠውነት ሙቀት መጠን ወትሮ ከነበረው ይጨምራል፡፡

- ብርድ ብርድ ማለት

- ማንቀጥቀጥ

- ማስቀመጥ

- የሆድ ድርቀት

- የአበጠው አፔንዲክስ ከፈረጠ ለተወሠነ ግዜ የህመሙ ስሜት ሊቀንስ ይችላል ነገር ግን ከላይ እንዳየነው ኢንፌክሽኑ እየተባባሠ ስለሚመጣ ከቆይታ በኋላ የህመሙ ስሜት እየጨመረ ይመጣል፡፡ በተለይም ህመምተኛው ሲራመድ ወይም ሲያስል የሚሠማው የህመም ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ ከላይ ያየናቸው የህመም ምልክቶች አንድ ጊዜ መታየት ከጀመሩ በኋላ ህመምተኛው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ይኖርበታል በተጨማሪም ምግብ መመገብ፣ ፈሣሽ ነገር መውሠድ የህመሙን ስሜት ሊያባብሰው ስለሚችል ይህንን ማድረግ የለብንም ማንኛውንም አይነት ማስታገሻ ወይም ፀረ-ተዋህሲያን መድኃኒቶችን ያላጤነ ባለሙያ ትዕዛዝ መቀም የለብንም ምክንያቱም እነዚህ መድኃኒቶች የህመሙን ስሜት በማጥፋት የሚደረግልንን ምርመራ ትክክለኛውን ውጤት እንዳያሣይ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ማንኛውም አይነት የጨጓራ ህመም ማስታገሻዎችን ወይም የድርቀት መድኃኒቶችን መውሠድ የለብንም በተጨማሪም ህመሙ የሚሠማን ቦታ ላይ ቀዝቃዛ ወይም ሞቃት ነገሮችን መያዝ አይኖርብንም፡፡

 

ምርመራዎች

 

የትርፍ አንጀት ህመምን ለመመርመርና በሽታውን ለማግኘት ህመምተኛው ላይ ሚያታዩትን ምልክቶች በደንብ ማየትና መረዳት ያስፈልጋል የተለየዩ አይነት በሽታዎች ልክ የትርፍ አንጀት አይነት የህመም ምልክቶችን ሊያሣዩ ስለሚችሉ ይህንን በደንብ ማጣራት ያስፈልጋል አንዳንድ ጊዜ ትርፍ አንጀት ነው ተብሎ የታሠበው ህመም በተለየዩ ምርመራዎች ሲጠራ ትርፍ አንጀት ላይሆንና የሌሎች በሽታዎች ምልክት ሊሆን ይችላል በዚህም ትርፍ አንጀት መከሠቱንና አለመከሠቱን ለማጣራት የሚደረገው ሂደት ቀላል አይደለም፡፡ በሽተኛው የሚያሣያቸው የህመም ምልክቶችን ቲፒካል (Typical) እና አቲፒካል (Atypical) ብለን ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

 

Typical Apendicitis (ትፒካል አፔንዲሣይትስ) የምንለው በሽተኛው በእምርቱ አካባቢ ለብዙ ሰዓታት የሚሰማ የህመም ስሜት ይኖረዋል የምግብ ፍላጐት መቀነስ ማቅለሸለሽና ማስመለስ ተያይዞ ይከሠታል፡፡ በመቀጠል የህመሙ ስሜት ወደ ቀኝ የታችኛው የሆድ ክፍል ይዞራል አካባቢውም በሚነካካበት ወቅት ጠጠር የማለት ስሜት ይኖረዋል፡፡

 

ሁለተኛውና አትፒካል (Atypical) የሚባለው የህመሙ ምልክቶች ከላይ እንዳየነው አይነት ምልክቶችን ለያሣዩ ይችላሉ የህመሙ ስሜት በቀጥታ በታችኛው ቀኝ የሆድ ክፍል አካባቢ ሊሠማ ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲከሠት በእርግጠኛነት ትርፍ አንጀት መሆኑን ለማጣራት አልትራሣውንድ ወይም ሲቲስካን መነሣት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በትርፍ አንጀት ምክንየት የሆድ ዕቃ ግድግዳ (peritoneum) በኢንፌክሽን ከተጠቃ የሆድ አካባቢ ጡንቻዎች በእጁ ሲነኩ የመኮማተር ሁኔታን ሊያሣዩ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች በፊንጢጣ አካባቢ ምርመራ ማድረጉ ጠቃሚና የተወሰነ ፍንጭ ሊሠጥ እንደሚችል ይጠቁማሉ ይኸውም የቀኙ የፊንጢጣ ክፍል በሚነካበት ወቅት ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠጠር የማለት ሁኔታ ሊኖረው ይችላል በአንፃሩ ደግሞ በፊንጢጣ አካባቢ ምርመራ ማድረጉ የሚያስገኘው ምንም የተለየ ውጤት እንደሌለ የሚገልፁ መረጃዎችም አሉ፡፡

የላቦራቶሪ ምርመራዎች

 የደም ምርመራ፡- በደም ምርመራ ወቅት የትርፍ አንጀት በሽተኞች ከፍ ያለ ነጭ የደም ሴል ቁጥር ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህ የነጭ የደም ሴሎች መጨመር በኢንፌክሽንና በሠውነት መቆጣት ምክንያት የሚከሠት ነው ነገር ግን እዚህ ጋር መገንዘብ ያለብን ነገር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የነጭ ደም ህዋሣት የትርፍ አንጀት በሽታ ብቻ ምልክት አለመሆናቸውን ነው ግን የተለያዩ አካላዊ ምርመራዎችን ከዚህ የደም ምርመራ ውጤት ጋር በማቀናጀት ጠቋሚ መረጃ ሊገኝ ይችላል፡፡

 የሽንት ምርመራ፡- በአብዛኛው ጊዜ በትርፍ አንጀት በሽተኞች ላይ የተለየ ውጤትን ላያሣይ ይችላል ነገር ግን አፔንዲክስ አብጦ በአካባቢው ካለው ፊኛ ጋር ፍትጊያን የሚፈጥር ከሆነ ለሽንቱ ላይ ደም ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሽንት ምርመራ ለሴቶች በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም አንዲት ሴት ከማህፀን ውጪ እርግዝና ከተከሠተበት ከላይ ያየናቸውን የትርፍ አንጀት ምልክቶችን ልታሣይ ትችላለች ታዲያ በሽንት ምርመራ ደግሞ እርጉዝ መሆኗንና አለመሆኗን ማረጋገጥ ስለሚቻል የሽንት ምርመራ ማድረጉ ይህንን ሁኔታ ለመለየትና ጥርጣሬ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡

 የሆድ አካባቢ ራጅ (X-ray) 10% የሚሆኑት የትርፍ አንጀት ታማሚዎቸ በዚህ የምርመራ ዘዴ ሲታወቁ በትርፍ አንጀት ውስጥ የተጠራቀመና ወደ ካልሲየምነት የተቀየረ ጠጠር ሠገራ (fecolith) ይታይባቸዋል፡፡ ይህም ምክንያቱን በቶሎ ለማወቅና አፋጣኝ እርምጃ ለመውሠድ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡

 አልትራሣውንድ (ultrasound) ይህ ዘዴ ያበጠውንና መጠኑ የጨመረውን አፔንዲክስ እንዲሁም በአካባቢው የተቋጠረውን ፈሣሽ ለማየት ይረዳል፡፡ በተጨማሪም በሴቶች ላይ ልክ እንደትርፍ አንጀት አይነት ህመምን ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ማህፀን፣ እንቁልጢ እና Fallopian tube(የሴቴ እንቁልጢ ቱቦ) የመሣሠሉት ላይ የሚከሠቱ የጤና ችግሮች እንዳሉና እንደሌሉ ለማጣራት ያስችላል፡፡

 CT-Scan (ሲቲ-ስካን) ይህ ዘዴ በአብዛኛው ጊዜ ሌሎች የምርመራ ዘዴዎችን ተጠቅመን ችግሩን በእርግጠኝነት ሣናገኘው ስንቀር የመንጠቀምበት ነው፡፡ ሲቲ-ስካን እስከ 95 በመቶ የሚደረስ የማጣራት ብቃት አለው፡፡ በዚህም አንድን ህመምተኛ በስህተት ለቀዶ ጥገና እንዳይዳረግ በከፍተኛ መጠን ይረዳል፡፡ በአሜሪካ በማሣቹሴት ጠቅላላ ሆስፒታል የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሣየው በተለያዩ ምርመራዎች ስህተት ምክንያት እስከ 20 በመቶ የሚደርሱ በሽተኞች ጤነኛ ኢንፔዲክስ እያላቸው ነገር ግን ትርፍ እንጀት ይዟችኋል፡፡ እየተባሉ ቀዶ ጥገና ያደርግላቸው ነበር ሲቲ-ስካንን መጠቀም ከተጀመረ በኋላ ግን ይህን ስህተት ወደ 3 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ ሲቲ-ስካን በሚጠቀመው ጨረር ምክንያት እርጉዞችና የህፃናት ላይ ለመጠቀም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳየነው ይህንን የትርፍ አንጀት ችግር መከሠቱንና አለመከሠቱን ለማወቅ ይህ ነው የሚባል አንድ አይነት ብቻ ዘዴ የለም ነገር ግን ከበሽተኛው የህመም ምልክቶች በመነሣት የተለያዩ የላቦራቶሪ ዘዴዎችን መጠቀም ይበልጥ ችግሩን ለይቶ ለማውጣት ይረዳል፡፡

 

ከትርፍ አንጀት ጋር ተመሣሣይ የህመም ምልክቶችን የሚያሣዩ ሌሎች ህመሞች

 

- በሌሎች ላይ የሚከሠቱ የእንቁልጥ፣ የማህፀንና Fallopian tube(የሴቴ እንቁልጢ ቱቦ) ላይ የሚከሠቱ ኢንፌክሽኖችና ዕጢዎች

- የአንጀት ቁስለት

- በፊኛ ላይ የሚከሠት ህመም፣ የጠጠር መፈጠር

- የሽንት ቧንቧ ኢንፎክሽን

- የቀኝ ኩላሊት ህመም በተለይም የኩላሊት ጠጠር

- የሀሞት ጠጠር

- በጉበት ላይ የሚከሠት ችግር

- ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሠ የጨጓራ ቁስለት

- በተለያዩ ባክቴሪያዎች አማካኝነት የሚከሠቱ የሆድ ዕቃ ውስጥ ኢንፎክሽኖች ናቸው፡፡

- በሴቶች ላይ ከወር አበባ ጋር የተያያዙ የህመም ስሜቶች

የትርፍ አንጀት ህክምናዎች

ህመሙ በተለያዩ ምርመራዎች ትርፍ አንጀት መሆኑ ከተረጋገጠ ህክምናው ቀዶ ጥገና ነው፡፡

 

ሁለት የተለያዩ አይነት ቀዶ ጥገና የማድረጊያ ዘዴዎች አሉ፡፡

 

 1. Appendectomy /አፔንዲክቶሚ/ ይህ የተለመደና በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ የቀዶ ጥገና ዘዴ ነው ይኸውም ከ2-3 /7.6 ሴሚ/ ኢንች የሚረዝም ክፍተትን በመፍጠር /በመቅደድ/ ትርፍ አንጀቱን የማውጣት ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ የሚከናወነው በሸተኛውን ሙሉ በሙሉ ሠመመን ውስጥ ለማስገባት ነው፡፡ የቀዶ ህክምናው ባለሙያ /ሰርጅኑ/ የበሸተኛውን ትርፍ አንጀት ካወጣ በኋላ በአካባቢው ኢንፌክሽን መፈጠሩንና አለመፈጠሩን ያጣራል፡፡ ኢንፌክሽን የፈጠረ ፈሣሽ በአካባቢው ላይ ከተቋጠረ ይህ ፈሣሽ በተለያዩ መንገዶች ከሠውነት እንዲወገዱ ያደርግና ክፍተቱ ተመልሶ ይሠፋል፡፡ አፔንዲክቶሚ በአጠቃላይ ከ1 ሰዓት ያልበለጠ ጊዜን የሚወስድ ሲሆን ነገር ግን ከፍተኛ ኢንፌክሽንና ተያያዥ ችግሮች በአካባቢው ከተፈጠረ የሚወስደው ጊዜ ከዚህ ሊረዝም ይችላል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሣዩነት ለምርመራ ስህተት የተነሣ ከ5 ህመምተኞች ውስጥ አንድ ትርፍ አንጀት ሣይኖርበት ቀዶ ጥገና ይደረግለታል፡፡
 2. Laparoscopic /ላፖራስኮፒክ/ ቀዶ ጥገና ይህ ዘዴ አዲስና በቅርቡ የተጀመረ ሲሆን በጣም ትንንሽ /መጠናቸው ከ0.25-0.5 ኢንች/ የሚደርሱ 3 ወይም 4 ቀዳዳዎችን ለመፍጠር ቀዶ ጥገናው ይከናወናል፡፡ Laparoscopic /ላፖራስኮፒክ/ የተባለ ዘመናዊ ቀጭን እላዩ ላይ ካሜራ የተገጠመላትን መሣሪያ በቀዳዳዎቹ በኩል በማስገባት የቀዶ ጥገናው ባለሙያ የበሸተኛውን ውስጣዊ ክፍል በማሣያው ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒውተር በደንብ ይመለከተዋል፡፡ ይህም ትርፍ ኢንጀቱንና በአካባቢው የተፈጠረውን ኢንፌክሽን በሚገባ አይቶ ቀጣይ ስራውን እንዲሠራ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ባለሙያው አይቶ ትርፍ አንጀት መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በቀዶ ጥገና መሣሪያው አማካኝነት ትርፉን አንጀት መጀመሪያ ላይ በተፈጠሩት ቀዳዳዎች በኩል እንዲወጣ ያደርገዋል ይህ ዘዴ አጠቃላይ ሠመመን ለበሰተኛው በመስጠት የማካሄድ ሲሆን እስከ 2 ሰዓት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ይህ የላፖራስከፒክ ዘዴ ከመጀመሪያው ጋር ሲነፃፀር የራሱ የሆኑ በጐ ጐኖች አሉት ከእነዚህም ውስጥ ከቀዶ ጥገና በኋላ የሚዩረው የቁስል ኢንፌክሽን እና የህመም መጠን ሊቀንስ ይችላል በተጨማሪም ከቀዶ ጥገና በኋላ የሆስፒታል የቆይታ ጊዜን ያሣጥራል፡፡ በዚህ ዘዴ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሰዎች በፍጥነት ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሠው ታይተዋል ቀድመውም በቆሎ የተለያዩ እስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል፡፡

ከህክምና በኋላ

ቀዶ ጥገናው የተካሄደው ያበጠው ትርፍ አንጀት ከመፍረጡ በፊት ከሆነ በሽተኛው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከህመሙ ያገግማል፡፡ ከቀዶ ጥገናው በኋላ በ1 ወይም 2 ቀናት ውስጥ ወደ ቤት ሊመለስ ይችላል፡፡ ከ2-6 ሣምንታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞው ሁኔታው ይመለሣል፤ ነገር ግን ያበጠው ትርፍ አንጀት ከፈነዳና በአካባቢው በሚገኘውን የሆድ ዕቃ ግድግዳ ላይ ኢንፌክሽን ካስከተለ ህክምናው ረዘም ያለ ጊዜን ሊወስድ ይችላል፡፡ ከቀዶ ጥገና በፊት በአካባቢው የሚገኘው በባክቴሪያ የተሞላ ፈሳሽ ከሠውነት እንዲወጣ ስለሚደረግ እና የተለያዩ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችም በደም ስር በኩል ለበሸተኛው ስለሚሠጡ የሆስፒታል የቆይታ ጊዜ ረዘም ሊል ይችላል፡፡ ከቀዶ ጥገና በኋላ ኢንፎክሽን በቦታው ላይ እንዲይፈጠር የሚታዘዙልንን መድኃኒቶች የህክምናው ባለሙያ ባዘዘልን መሠረት በአግባቡ ሣናቋርጥ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ በአጠቃላይ የጤና ባለሙያው የሚሠጠንን የአመጋገብና የእንቅስቃሴ መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረጉ በቶሎ ለማገገም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከቀዶ ጥገና የማገገሚያ ጊዜ እንደዕድሜ ሁኔታ የሠውነት በሽታን የመከላከል አቅምና እንደ ችግሩ ስርመስደድና አለመስደድ የተለያየ ነው፡፡

ከህክምና ተቋማት ከወጣን በኋላ የሚከተሉት ሁኔታዎች ከተከሠቱ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት ተመልሶ መምጣት ያስፈልጋል፡፡

 

ቀዶ ጥገናው የተደረገበት አካባቢ ከፍተኛና ፊታ የማይሠጥ ድንገተኛ ህመም

ደም ማስቀመጥና ማስመለስ ካለ

የመደንዘዝና ራስን የመሣት ስሜት

ለመቆጣጠር አደጋች የሆነ ማስቀመጥና ማስመለስ

በቀዶ ጥገናው ስሜት አካባቢ ፈሣሽ የመቋጠርና በጣም የማበጥ ሁኔታ

ምክንያቱ ያልታወቀ ከፍተኛ የሠውነት ሙቀት መጠን፡፡

 ትርፍ አንጀት እንዳከሠት አስቀድሞ መከላከል ይቻላልን?

የተለያዩ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ይህንን ዘዴ በመጠቀም ትርፍ አንጀትን መከላከል ይቻላል፡፡ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ አብዛኞዎቹ ግን በአሠር ወይም (Fiber) የበለፀጉ አታክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ መመገቡ በአንጀት ውስጥ ጠጣር የሆነ ሠገራ መጠራቀም እንዳይከሠት ስለሚያደርጉ በተወሠነ መልኩ ችግሩን ሊቀርፈው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የተለያዩ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ይህንን ዘዴ በመጠቀም ትርፍ አንጀትን መከላከል ይቻላል፡፡ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡

Albert Einstein

Follow Us

Subscribe Our Newsletter

Amazing Deals, Updates & Freebies In Your Inbox

MEDICAL's Poll

Which hospital is the best in 2019?
logo

Download Newskit App

Lorem Ipsum is simply dummy text of the printing and
typesetting industry.

banner

Social & newsletter

Search